Logo for SMNE Solidarity Movement for a New EthiopiaContact usAmharic information
Humanity before Ethnicity

የማያቋርጥ የደወል ጥሪ [ተለዩ]


በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የጭቆና ጠፍሩን አጥብቆ ላለፉት 20 ዓመታት የአፈና ስርዓቱን የዘረጋው ህወሃት/ኢህአዴግ የፈፀማቸው አስከፊ ተግባራትና ሊረሳ የማይችል ታሪካዊ ስህተት ከግብረ አበሮቹ ጋር ለፍርድ የሚቀርብበት  ቀን እየተቃረበ መሄዱ ማንም የሚክደው ሃቅ አይደለም፡፡ ሆኖም የጋራ ንቅናቄያችን የቆመበት መሰረቱ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ መሰጠት በመሆኑ ወደፊት ሊፈጠር የሚችለው እጅግ ያሳስበዋል።

በዚሁ ሰብዓዊነትን በሚያስቀድመው የዕምነታችን መሰረት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የህወሃት/ኢህአዴግን  የአፈና ጡንቻ በማፈርጠም ራሳቸውንም ሆነ ወንድምና እህቶቻቸውን፣ እናትና አባቶቻቸውን፣ ታናናሽ ልጆቻቸውንና መተኪያ የሌላት አገራቸው ላይ እየተፈፀመ ላለው አስነዋሪ ግፍ ተባባሪ የሆኑ የስርአቱ ታዛዦችን ከማይቀረው ፍርድ ለመታደግ ድርጅታችን ወሰን።

የጋራ ንቅናቄያችን ሥራ አስፈጻሚ በጥፋት ጎራ የተሰለፉት ዜጎች ወደ ልባቸው  በመመለስ ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ውስጥ በህቡዕ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ ባሉበት ሆነው በልባቸው ስርዓቱን እንዲለዩ፣ መከፈል ያለበትን ዋጋ እንዲከፍሉና በነሱ ድጋፍ የፈረጠመውን የህወሃት/ኢህአዴግ ስርዓት የአፈና ጡንቻ እንዲያኮሰምኑ ጥሪ እንዲተላለፍላቸው አሁንም ለሰብዓዊነት ካለው የቀደመ ዓላማው በመነሳት ተስማማ።

በዚሁ ስምምነት መሠረት የጥሪውን መልዕክት ታስተላልፍ ዘንድደወልተፈጠረች።

ለህወሃት/ኢህአዴግና በአምሳያው ለተፈጠሩት ድቃይ ድርጅቶች የፖሊት ቢሮ አባላት፣ ለክልል መስተዳድር ኃላፊዎች፣ ለሚኒስትሮች፣ ለአምባሳደሮችና የየኤምባሲው ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ለቢሮ ኃላፊዎች፣ ልማታዊ ባለሃብቶች፣ ለተለያዩ የመዋቅር መሪዎች፣ ለወጣት ክንፎች፣ ለዞንና መንግሥታዊ ተቋማት፣ ወዘተ የአደረጃጀት እርከኑን በመከተል ደወል በየሳምንቱ ትደርስ ጀመር። ደወል ያፈራችውን ፍሬ ለጊዜው መዘርዘሩ ባያመችም የደወልን ጥሪ የተቀበሉና ለደወል ጥሪ ምላሽ የሰጡ ጥቂት እንዳልሆኑ ከድርጅታችን የህዝብ ግንኙነት ግብረኃይል የአፈጻጸም ሪፖርት ተረድተናል።

የደወልን መልዕክት የተቀበሉ ያሉትን ያህል፣ ጥሪው ያስደነገጣቸው “አውራ” አመራሮችና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳይ ፅህፈት ቤት ለጋራ ንቅናቄያችን ዋና ዳይሬክተር አዲስ “የፖለቲካ ሹመት” በመስጠት ድርጅታችን አጥብቆ የሚጸየፈውንና የሚኮንነውን የሽብርተኛነት ታፔላ ለጥፈዋል። ድርጅታችን የእንዲህ ዓይነቱ ፍረጃ መነሻ በውል ስለሚረዳ አይሸበርም። ይልቁኑም አዲሲቷ ኢትዮጵያን ለማየት ካለው ታላቅ ራዕይ አንጻር የጀመረውን ትግል፣ የዓላማው የመሰረት ድንጋይ የሆነውን ከዘር ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጠውን መርህ ከፍ በማድረግ ይቀጥላል። ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለፍትሕ መስፈንና ለዕርቅ ይሟገታል።

በመሆኑም የጀመርነው አገርን የማዳንና የኢትዮጵያን መከራ የማሳጠር ትግል ከማጠናከር አኳያ እስካሁን በደወል ቁ.1 - ቁ.10 ያስተላለፍነውን ወገናዊ ጥሪ መላው ኢትዮጵያዊ እንዲያውቀው እንደሚከተለው በይፋ አቅርበነዋል። አገር የምትድነውና የምታድገው በዜጎቿ ቀናና በጎ ኅብረት በመሆኑ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጠውን የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ግንባታ እናፋጥን ዘንድ የደወል መልዕክት የአመለካከትና የፖለቲካ ድንበር የለውምና ለሁላችንም አገር ወዳዶች ነው።

የደወል ጥሪ መቼም የሚያቆም አይደለም፡፡ በአገር ውስጥ እጅግ በርካታ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ጋር በተለያየ መስኩ ያለንን የጠበቀ ግንኙነት አጠናክረን በመቀጠል ከዘረኝነት ይልቅ ሰብዓዊነትን መሠረት ያደረገች አዲሲቷ ኢትዮጵያን ለመመሥረት ትግላችን ይቀጥላል፡፡ ከአገር ውስጥና ከውጪ በሚደርሱን መረጃዎችና የድጋፍ ዕርዳታዎች አጋዥነትም የደወል ጥሪ በተለያየ መልኩ ይቀጥላል፡፡

ደወል ቁ.1 - ቁ.10 ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡


 View article in Word                 return to top                  View article as a PDF