Logo for SMNE Solidarity Movement for a New EthiopiaContact usAmharic information
Humanity before Ethnicity

ደወል
ቁጥር 1


ዝናውም፣ ክብሩም፣ ሃብቱም፣ ሁሉም ያልፋል። ጊዜም ከጥላችን ይልቅ ይበራል። ደጎች ላገራቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለተተኪው ትውልድ መልካም ነገር አስቀምጠው ሲያልፉ በበጎ ሲታወሱ ይኖራሉ። የክፉ ታሪክና ልምድ ማጣቀሻ ከመሆን ለአገርና ለወገን መልካም ስራ ሰርቶ ማለፍ ያኮራል።

ዓለም አምባገነኖችን ተፀይፋለች። የተረገጡ ህዝቦች ጎዳና ሞልተው አምባገነኖችን እስከወዲያኛው ለመቅበር የሚደርጉት የሞት ሽረት ትንቅንቅ ተጧጡፏል። የዓለም ኃያላን አገሮችም አምባገነኖችን “ሥራችሁ ያውጣችሁ” እያሏቸው ይገኛል። በሌሎች አገሮች የታየው የአምባገነኖች መጨረሻ የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥም እንደማይቀር በርግጠኛነት እንነግርዎታለን።

እርስዎ ይህ አገዛዝ ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈጸመውንና እየፈጸመ ያለው አስነዋሪ በደል ማብቃት አለበት ከሚሉ ዜጎች መካከል የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ነዎት። ታዲያ ቤተሰቦችዎ፣ የሥራ ባልደረቦችዎ፣ ጎረቤቶችዎ ወዘተ ይህንን አገዛዝ በማገልገልዎ መጠቋቆሚያ እያደረጉዎት እስከመቼ ይኖራሉ? ደርግ በ1981 ብሔራዊ እርቅ እንዲያደረግ ሲለመን አሻፈረኝ ብሎ ታሪኩን በውርደትና ባሳፋሪ ታሪክ ጠቀለለው። “አንደፈርም!” ሲሉ የነበሩት እንደጉም ተበተኑ፤ በእስር ቤት ማቀው የቁም ሞት ሞቱ፣ በሽተኛ ሆኑ፣ አስከሬናቸው ከከርቸሌ ወጣ። ዛሬስ? ዛሬማ አይደፈሩም የተባሉ አምባገነኖች በሕዝብ ዓመፅ በቀናት ውስጥ ተሽመድምደው ሲወድቁ ታንክና ቦንብ ሊያድናቸው እንዳልቻለ አይተናል።

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ላይ የአንድ ብሔር የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ስለመስፈኑ፣ አቤት የሚባልበት ነፃ የፍትህ ተቋምና ሥርዓት ስላለመኖሩ፣ ዜጎች የሚናገሩበትና የሚተቹበት እንዲሁም በተቃውሞ ሀሣባቸውን የሚገልፁበት የፖለቲካ ምህዳር አለመኖሩ የሚታወቅ ነው። ሌላው ቀርቶ የኢህአዴግ አባል ሆነው በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ የሚንፀባረቁ ቅሬታዎችን፣ አስተያየቶችንና የተቃውሞ ሃሣቦችን ወደ መድረክ አውጥተው እንዳትወያዩ እውነታዎችን ለውይይት የሚያቀርቡ ግለሰቦችን ቅስም በሚሰብር ወይም በፍርሃት በሚያሸማቅቅ ሁኔታ በመተቸት ከዚህ ባለፈም በቀልን ባነጣጠረ የቡድን ግምገማ አዋክቦ በመወንጀል ለእንግልት፣ ለስደት፣ ለእስር፣ ድብደባና ግድያ የሚዳረጉበት ሁኔታ እንደሰፈነ ከእርስዎ የተሰወረ አይደለም።

ዛሬ ማንኛውንም የልዩነት ሃሣብ በኢህአዴግ አባልም ሆነ በተቃዋሚ ኃይሎች ሲቀርብ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት፣ የአናርኪነት ፍጥጫ ብሎም የሽብርተኝነት ዓላማ እያስመሰሉ ከማቅረብ አልፎ ስለ ስኳር መጥፋት፣ ስለ ዘይት መወደድ፣ ስለ ፍትሕና መልካም አስተዳደር መጥፋት፣ ስለ ነጻነት መታጣት፣ ስለ ምርጫ መጭበርበር፣ ስለ ሙስና መስፋፋት ሁሉ ሲነሳ “ይህ የኒዎሊበራል አመለካከት ነው!!” ወይም “ይህ የፀረ ህዝቦች ፕሮፓጋንዳ ነው!!” የሚል ማስፈራሪያ ማሰማትና የ“እርምጃ” ይወሰዳል ዛቻ ማስቀደም ዕለታዊ ክስተቶች ሆነዋል።

በኢህአዴግ ህዋሶች ውስጥ በአዲስ ራዕይ መፅሔት፣ በህዳሴ ጋዜጣና በመሳሰሉት ልሳኖች ለውይይት የሚቀርቡልዎ ርዕሶች ከግል ቤተሰብዎ ጀምሮ ለእርስዎና በዙሪያዎ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ብሎም የአገሪቱን ችግሮች በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን የህወሃት/ኢህአዴግና የሌሎቹ ድቃይ ድርጅቶቹ አመራሮች የአገዛዝ ዘመናቸውን ለማራዘምና ለግል ጥቅማቸው ማስፈፀሚያ ፍጆታ ይውል ዘንድ ለሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ታዳሚና ነጋሪ ሊያደርግዎ እንጂ አንዳች ረብ ያለው እንዳልሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁት ሐቅ ነው::

ታዲያ እስከ መቼ ድረስ ለዚህ ሥርዓት ሎሌ ሆነው ይቀጥላሉ? የሕዝብ ምሬት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚለወጥበት ጊዜ ዕውን እየሆነ ነው፡፡ ይህ እውነት ሲከናወን የማሰቢያም ሆነ የንስሃ ጊዜ የለም። “ሆድ ይፍጀው” የሚባልበት ዘመንም አልፏል።

ስለሆነም ዛሬ ከስር እያደጉ ያሉ ወንድሞችዎ፣ እህቶችዎ፣ እናትና አባትዎ እንዲሁም ዘመዶችዎ በአጠቃላይ የአገሪቱ  ዜጎች ፍትህና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ አድሎአዊነት የሌለባት በኢህአዴግ አባልነታቸው ወይም ከአንድ ውስን ጎሣ በመወለድ ብቻ ለፖለቲካ ተሣታፊነት፣ ሰርቶ ለመኖር፣ አምርቶ ለመብላትም ሆነ ሀብት ለማፍራት በአገሪቱ የሚገኝ ዕድል ያለአድልኦ እኩል ተካፋይነት የሚኖርባት አዲሲቱን ኢትዮጵያ የመፍጠር ኃላፊነት አለብዎ፡፡

ስለዚህ “ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንስጥ” እንዲሁም “ሁላችንም ነፃ ካልወጣን ማንም ነፃ አይሆንም” በሚል መርሆ የተመሠረተውና በአገራችን ፍትሕ፣ ሰላም፣ አንድነትና ዕርቅ እንዲሰፍን ከሚታገለው “ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ” ጋር እንዲቆሙ ይህንን የጥሪ ደወል እናሰማለን።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ

ሌሎቹን የደወል ጽሑፎች ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡


 View article in Word                 return to top                  View article as a PDF