Logo for SMNE Solidarity Movement for a New EthiopiaContact usAmharic information
Humanity before Ethnicity

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሕዝባቸው ጋር ሊገናኙ ይገባል!


ቀን፤ ነሐሴ 11፤ 2010ዓም
ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በተደጋጋሚ ከሕዝብ ጋር ቀጥተኛ ሲያደርጉ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝባቸው ጋር ግንኙነት ሳያደርጉ ሁለት ሳምንታት አልፈዋል። ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተለው ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የጠ/ሚ/ሩ ደጋፊዎችና መላው ሕዝባችን ሁኔታውን እንዲያውቅና አስፈላጊውን ውሳኔ እንዲወስድ ይፋ ለማድረግ ተገድዷል። በእርግጥ ዶ/ር ዐቢይ በተቀነባበረ በሚመስል ስልት ሁለት ሦስት ጊዜ ያህል ለሕዝብ ዕይታ ቀርበዋል። ሆኖም ከወትሮው በተለየ መልኩ ለውጡን አጥብቀው የሚቃወሙና ለማክሸፍ የሚፈልጉ ኃይሎች ያቀነባበሩት በሚመስል የተከናወነው ከሚዲያ ፍጆታ የማያልፍና በጥያቄ ውስጥ ያለውን ሕዝብ ለማርገብ የተሰራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ሆኖ ነው ያገኘነው። ስለዚህ ሕዝባችን መሪውን የማግኘትና የማነጋገር መብቱ ሊነፈግ አይገባም፤ ይህም ባጭር ጊዜ ውስጥ በጋዜጣዊ መግለጫም ሆነ በፊት ሲደረግ እንደነበረው ዓይነት የውይይት መድረክ መገለጽ ይገባዋል በማለት አኢጋን አቋሙን በግልጽ ያስታውቃል።  

  ከዚህ በፊት “የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ በየሰዓቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መገለጽ አለበት፤ ከእንግዲህ በኋላ በኢትዮጵያ የድብቅ ፖለቲካ አበቃ፤ …. የእኔ ሥራ የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት … ማስፈጸም ብቻ ነው” የሚል ቃል የገቡልን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም የመደበቅ እና የመሸረብ ፖለቲካ ማብቃቱን ያበሰሩልን መሪያችን ሕዝብ እንዲህ ተጨንቆና ባገሩ ላይ የመኖር ኅልውናው አደጋ ላይ ወድቆ ባለበት ወቅት ከሕዝባቸው ጋር እንደበፊቱ እንዳይነጋገሩ የገደባቸው ኃይል ምንድነው? የጉራጌና የቀቤና ሕዝብ በተጋጨበት ወቅት በፍቅር ተግሳጽ ታረቁ ብለው መክረው ወዲያው ያስማሙ ብልሃተኛ ከሕዝባቸው ጋር እንዳይመክሩ የኅሊና እስረኛ ያደረጋቸው ማነው? ተስፋ በሚሰጠውና የወደፊቱን ብሩህ አድርጎ በሚያሳየው አንደበተ ርዕቱነታቸው ሕዝባቸውን እንዳያረጋጉ አጣብቂኝ ውስጥ የከተታቸው ጉዳይ ምንድነው? ይህንን የሕዝብ ጥያቄ የጋራ ንቅናቄያችን ሕዝብ እንዲያውቀው ይፋ ለማድረግ ተገድዷል።

እጅግ በርካታ የሰቆቃና የመከራ ዓመታትን ያሳለፈው የአገራችን ሕዝብ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና እርሳቸው በሚመሩት ቡድን አማካኝነት ያገኘው ለውጥ ጥቂት ከሚባሉ ቡድኖችና ግለሰቦች በስተቀር በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ ያልጠበቀውን ተስፋ ያጎናጸፈው ነው። በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ አሠራር እያስተዳደሩን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በየጊዜው ባለማቋረጥ ለሕዝባችን የሰጡት ተስፋና ባጭር ጊዜ ውስጥ የፈጸሟቸው ተግባራት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙትም አገራት ታስቦ የማታወቅ ለውጥ ያመጣ ነው።

ሆኖም ግን ዶ/ር ዐቢይ የአሜሪካ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል፤ እርሳቸውም እንደቀድሞው ከሕዝባቸው ጋር የሚደርጉትን ግንኙነት በእጅጉ ቀንሰዋል። በእርግጥ ዕረፍት ዐልባ በነበረው የአሜሪካው ጉብኝታቸውና ከዚያ በፊት በነበሯቸው ጊዜያት ያለበቂ ዕረፍት መሥራታቸው፤ በጤናቸው ላይ መቃወስ ሊያስከትል እንደሚችል ማንም መገመት ይችላል። ሆኖም ዝምታቸውን ተከትሎ የወጡ ሕዝብን የሚረብሹና የለውጡ ተቃዋሚዎችን የሚያበረታቱ ዘገባዎች ሊወገዙ የሚገባቸው ናቸው። ጊዜያዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ከማሰብ በፊት እንደ ሚዲያ የአገርን ኅልውና፣ የጠላትን አካሄድ፣ የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም ተገቢ ነውና የጋራ ንቅናቄያችን በዚህ ላይ ትኩረት እንዲደረግበት ያሳስባል፤ ሕዝባችንም ምርቱን ከግርዱ እየለየ መረጃ የመቀበል ባሕሉን በማዳበር ለእንደዚህ ዓይነት ዘገባዎች ዕውቅና መንፈግ ይገባዋል። ጸረለውጥ የሆኑ ዘገባዎችንም እንዲሁ ዓላማቸውን አውቆ በመልሶ ማጥቃት ሊቃወማቸው ይገባል።

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ወደአገር ከተመለሱ ሁለተኛ ሳምንት አልፏቸዋል። በእነዚህ ሳምንታት ውስጥ በርካታ የሚረብሹና የሚያስጨንቁ ሁነቶች ተከስተዋል። ለአብነት ያህል፤ እርሳቸው በወጡ በማግስቱ በግፍ ከተገደሉት ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር) በኋላ በርካታ አለመረጋጋቶች በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ታይተዋል። አሁን እየተረጋጋ ነው በሚባልበት የሶማሊ ክልል በርካታዎች ከመገደላቸውና ከቀያቸው ከመፈናቀላቸው ባሻገር እጅግ ባልተለመደ ሁኔታ እስከ 10 የሚደርሱ አብያተ ክርስቲያናት ወድመዋል፤ ካህናት ተገድለዋል፤ ሻሸመኔ ላይ በሐሰት በተሰራጨ ወሬ አንድ ወገናችን ላይ በቃላት ለመግለጽ የማይቻል አሰቃቂ ተግባር ተፈጽሞበታል፤ በምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ ከሶማሊ ክልል ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘና በሌሎች ሰበቦች በርካታ ወገኖች ከቤታቸው እየተፈናቀሉ ነው፤ ቤት ንብረታቸው እየወደመ ነው፤ ሕይወታቻውን ለማዳን የለበሱትንና ልጆቻቸውን ብቻ ይዘው እየሸሹ ነው፤ ከጅጅጋ አካባቢ ተፈናቅለው ሕይወታቸውን አትርፈው አዳማ (ናዝሬት) የደረሱ ወገኖች እዚያም እየተገደሉና መግቢያ እንዲያጡ እየተደረጉ ነው፤ የኢትዮጵያ ሶማሊ ተወላጅ ያልሆኑ በድሬዳዋና አካባቢው የሚገኙና ከጅጅጋ ተሰደው የመጡ በሶማሊ ልዩ ፖሊስና በሄጎዎች ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ህጻናት ሳይቀሩ ተገድለዋል፤ ቤ/ክ የተጠለሉ እርጉዞችንና እመጫቶችን ጨምሮ በርካታዎች ከዚያ እንዳይወጡ ተደርገው ምግብና ውሃ በማጣት ስቃይ ተዳርገው ከቆዩ በኋላ ስቃዩ በዝቶባቸው ለልጆቻቸው ውሃ ለማጠጣት የወጡ እናቶች ተገድለዋል፤ የተጠለሉበትም ቤ/ክንም ተቃጥሏል፤ በጅጅጋ የነበረው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽ/ቤትም ጥቃት ደርሶበት መረጃዎችና ሰነዶቹ ከነኮምፒውተሮቹ ተዘርፈዋል፤ ጽ/ቤቱም ወድሟል፤ በጅቡቲ በሰላም ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የጥቃት ሰለባ ሆነው 30ሺህ የሚሆኑ ወገኖቻችን ከጅቡቲ ለቅቀው ወጥተው በውሃ ጥምና በምግብ ማጣት እየተሰቃዩ ይገኛሉ፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በቴፒ ከተማ በተፈጠረ ሁከትና እስካሁን ባላቆመ ጥቃት ወገኖች እየተገደሉ ነው፤ የጌዲኦን ተፈናቃዮች ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ውስጥ በተፈጠረ አለመረጋጋት በሰላም ከሚኖሩበት ቀዬ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

በምስራቁ የአገራችን ክፍል እየደረሰ ያለውን በተመለከተ መንግሥት ሁኔታዎች እየረገቡ ነው ቢልም ዋንኛ የጥፋት ኃይል የሆነውን የሶማሊ ልዩ ፖሊስን ትጥቅ ስለማስፈታት የሚነገር አለመኖሩ “ለምን?” የሚል ጥያቄ እንድናነሳ የሚያደርገን ሆኗል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ይህ ሁሉ ሲሆን የእናቶችን እንባ በተግባር ሲጠርጉና ለወገናቸው ደም ሲለግሱ በገሃድ የታዩት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ዝምታ መምረጣቸው የእርሳቸው ባህርይ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። “ልሞትልህ የተዘጋጀሁ ነኝ” ያሉት ሕዝባቸው “ወዴት እየሄድን ነው? አገራችንስ ወዴት እየሄደች ነው?” የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች ተወጥሮ ባለበት ሁኔታ (ለሁሉም ነገር እርሳቸው እየተጠየቁ መልስ መስጠት አለባቸው ባንልም) በአስገዳጅ አጣብቂኝ ውስጥ ካልገቡ በስተቀር ሕዝባቸውን ዝም ሊሉት እንደማይችሉ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ያምናል። ለጋራ ንቅናቄያችን ከሚደርሱን መረጃዎች በመነሳት ይህንን እምነት ሕዝባችንም ይጋራል ብለን እናምናለን።

ስለዚህ እነዚህንና ከላይ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ቀላሉ መንገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው የአገር ውስጥና የውጪ ጋዜጠኞችን ሰብስበው ያልተገደበ ነጻ መገለጫ መስጠት ይገባቸዋል እንላለን። ከሕዝቡ ጋር አንዳንድ ጊዜ በቀን ከሁለት ጊዜ በላይ ሲገናኝ የቆየ መሪ ኮሪደር ላይ በማነጋገርና ቪዲዮ በመልቀቅ  ወይም ሕዝብ መግቢያ መውጫ አጥቶ በተጨነቀበት ጊዜ ከቡና ላኪዎች ጋር ተገናኘ ብሎ ዜና በመሥራት “ደኅንነቱን” ማሳየት የዶ/ር ዐቢይን ባህርይ የሚገልጽ አይደለም፤ ማንም ሊቀበለው የማይችል ጊዜ መግዣ ነው።

ስለዚህ ይህንን የሕዝብ ጭንቀት ከላይ በጠቀስነውና ባልተገደበ መልኩ በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ፤ ሕዝብና መሪው እንደቀድሞው እንዲገናኝ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ያሳስባል።
ፈጣሪ የአገራችንን ሰላም ያጽናልን፤ ሕዝቧንም ይባርክ።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)

 View article in Word            return to top             View article as a PDF